በትግራይ ክልል 80 በመቶ የኢንዲስትሪዎችና የአገልግሎት ሠራተኞች ከሥራ ውጪ መሆናቸው ተገለጸ
በናርዶስ ዮሴፍ
8 Nov 2023
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ያቋቋመው ‹‹በትግራይ የተፈጸመ ዘር ማፅዳት አጣሪ ኮሚሽን›› በ11,312 የግል የኢንዱስትሪዎችና የአገልግሎት ተቋማት ላይ አደረግኩት ባለው ጥናት፣ በጦርነቱ ምክንያት በኢንዱስትሪዎች 80 በመቶና ከአገልግሎት ዘርፉ ደግሞ 70 በመቶ ያህል ሠራተኞች በተለያዩ አጋጣሚዎች ከሥራ ውጪ መሆናቸውን እንዳጋጠማቸው አስታወቀ።
በሁለቱ ዘርፎች ላይ የተደረገው ጥናት በጦርነቱ ምክንያት የደረሰ ቀጥተኛ ውድመት፣ በውድመቱ ምክንያት የመጣ ኪሳራንና መንገዶች በመዘጋታቸውና የግንኙነት መስመሮች በመቋረጣቸው የደረሰ ጉዳትን የሚያካትት መሆኑን ኮሚሽኑ ለሪፖርተር ገልጿል።
ውድመቶቹ በአንድ በኩል በንግድ ተቋማት ላይ የደረሱትን፣ በሌላ በኩል በተቋማቱ ላይ የደረሰው ጉዳት በሕዝቡና በአካባቢው ላይ የፈጠራቸው ችግሮች በሚል መለየታቸውን ገልጿል፡፡
ኮሚሽኑ ከሰው ኃይል ጋር በተያያዘ የደረሰበት ውጤት ከጦርነቱ በፊት በ4,180 የንግድ ተቋማት ውስጥ 99,604 ሠራተኞች በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ተቀጥረው ይሠሩ የነበረ ቢሆንም፣ በአሁኑ ጊዜ ይህ ቁጥር ወደ 17,604 ወርዶ መገኘቱን ጠቁሟል።
በአገልግሎት ዘርፍ ደግሞ በ7,132 ተቋማት ላይ ጥናት መደረጉንና ከጦርነቱ በፊት ከነበረው 35,692 የሥራ ኃይል ውስጥ 70 በመቶ ያህል በተለያየ ምክንያት ከሥራ ውጭ መሆኑን እንዳረጋገጠ ተናግሯል፡፡
የኮሚሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ የማነ ዘርዓይ፣ ‹‹ተቋማቱ ሥራ ስለማይሠሩ ያሰናበቱዋቸውን ሠራተኞች ብቻ ሳይሆን የሞቱ፣ የቆሰሉና፣ የጠፉ ሠራተኞችም ይጨምራል፤›› ሲሉ ለሪፖርተር ተናግረዋል።
‹‹በግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ወደ ሁለት ሺሕ የሚሆኑ ተቋማት ላይ ጥናት አካሂደናል ያሉት ኃላፊው፤››፣ ‹‹ከእነዚህ ውስጥ የሞቱ፣ የቆሰሉ፣ አካላቸው የጎደለ ወይም የጠፉ ሠራተኞች በሚል ዝርዝር ውስጥ ተካተው በሥራ ገበታቸው ላይ እንደሌሉ ያረጋገጥናቸው 1,653 ሠራተኞች ናቸው፤›› ብለዋል። የግብርናው ኢንቨስትመንት ዘርፍ በአጠቃላይ 49 ሺሕ ሠራተኞች የነበሩ ቢሆንም፣ ከጦርነቱ በኋላ ግን 1,343 ሠራተኞች ብቻ በሥራ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በትግራይ ክልል በኢንዱስትሪ፣ በአገልግሎትና በግብርና ዘርፎች ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ በነበሩት ዓመታት በደረሰው ውድመት ምክንያት፣ ኢትዮጵያ ከግብርና ምርቶች የወጪ ንግድ ማግኘት ከነበረባት የውጭ ምንዛሪ ያጣችው ምን ያህል እንደሆነ ጥናቱ ሲጠናቀቅ ይታወቃል ተብሏል።
ኮሚሽኑ በጥቅሉ በጦርነቱ በሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በትግራይ ክልል ላይ የደረሱ ጉዳቶችን ለማጣራት፣ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር መቋቋሙ ይታወሳል።
ከትግራይ ክልል አጠቃላይ የቆዳ ስፋት 45 በመቶ በሚሆነው ክፍል ላይ ከየተደረገ ያለው ምርመራ፣ በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን፣ ፆታዊ ጥቃቶችን፣ በኢኮኖሚ ላይ የደረሱ ውድመቶችን፣ የመሠረተ ልማት ጉዳቶችን፣ በማኅበራዊ ተቋማት ላይ የደረሱ ጉዳቶችን፣ በአካባቢያዊና በተፈጥሯዊ ሀብቶች ላይ የተፈጸሙ ጥፋቶችን መጠን ለማወቅ እንደሚካሄድ ከኮሚሽኑ ለመረዳት ተችሏል።
ምርመራው በየቤቱ ነዋሪዎችን በማነጋገር፣ የግል የንግድ ተቋማትንና የመንግሥት የሥራ ተቋማትን ለየብቻ በማጥናት እንደሚከናወንም ተገልጿል፡፡ ከሰብዓዊ መብት ጋር በተያያዘ ካሉት ሁለት ጥናቶች በተጨማሪ፣ በተቀሩት ላይ ማለትም በማኅበራዊና በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ኮሚሽኑ እያደረገ ያለውን ጥናት ከሁለት ሳምንታት በኋላ ለሚመለከታቸው የፌዴራልና የመንግሥት አካላት፣ እንዲሁም ለዓለም አቀፍ ተቋማት ለአስተያየት ካቀረበ በኋላ፣ ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግ የኮሚሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ የማነ አስረድተዋል።
‹‹ጥናቱ ሙሉ ትግራይን እስኪሸፍን ድረስ መቀጠል አለበት፡፡ ምክንያቱም ትግራይ ክልል ውስጥ አካባቢን ወይም ሰውን ሳይመርጥ ሁሉም ቦታ የደረሰ ስለሆነ ነው፤›› ብለዋል።
እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ማብራሪያ፣ የኮሚሽኑ ግኝቶች በሰብዓዊ መብት በኩል ለሕግና ለሽግግር ፍትሕ ለሚጠቀሙ እንዲሁም በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በአካባቢያዊ በኩል ደግሞ ለማገገም (recovery)፣ መልሶ ለማቋቋም (rehabilitation) እና ለመልሶ ግንባታ (reconstruction) መነሻ ይሆናሉ ተብሎ ይታመናል፡፡
‹‹የማኅበራዊና የኢኮኖሚያዊ ውድመት ውጤቱ ወደ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ምርመራ ግኝት ለመሸጋገር ቅድመ ሁኔታ አድርገን ብናየውም፣ ፍትሕ ገንዘብ ስለተሰጠ ብቻ በቂ አይሆንም፤›› ብለዋል። ‹‹በሰብዓዊ መብት ጥሰት ምርመራዎቻችን ግኝት ማንና የትኞቹ ጥፋቶች ለይቅርታ፣ የትኞቹን ለመማር፣ በየትኞቹ ላይ ፍትሕ መሰጠት አለበት በሚሉና ለየትኞቹ ደግሞ ካሳ እንደምንጠይቅ እየለየን ነው፤›› ሲሉም አስረድተዋል።
Source: The Ethiopian Reporter